"በክልል ደረጃ ቅሬታ ሲቀርብ የመጀመሪያው ነው" የምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ

ሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ቢሮ Image copyright NEAEA

የሃገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ይፋ ከተደረገ አንስቶ የተለያዩ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው። ቅሬታው የጀመረው በፈተናው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሳይቀሩ ስኮላስቲክ አፕቲቱዩድ በሚባል የፈተና ዓይነት ዝቅተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው ነው።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተናው ውጤት ላይ ቅሬታ እንዳለው አስታውቋል። የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮም በፈተናው ውጤት ላይ ቅሬታ እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በበኩሉ የአፕቲቲዩድ ፈተና ውጤትን የሚያጣራ ኮሚቴ ማዋቀሩን ተናግሯል።

የትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ላይ ቅሬታ አቀረበ

የስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና ውጤትን የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቀረ

ያነጋገርናቸው በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ረዲ ሺፋ ዛሬ እንደገለፁልን "በክልል ደረጃ ቅሬታዎች ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።

አቶ ረዲ ሺፋ እንደሚሉት የፈተና ማረሚያ ሶፍትዌሩና የማረሚያ ማሽኑ ከእንግሊዝ አገር የመጣ ሲሆን አገልግሎት መስጠት ከጀመረም ዓመታት እንደተቆጠሩ ያስረዳሉ።

ይህ ማሽን ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ 'ኮብል' የሚባል ሶፍትዌር ለፈተና ማረም አገልግሎት ይውል እንደነበር ያስታውሳሉ።

ኤጀንሲው የሚዘጋጀው የ10ኛ ክፍልን አገር አቀፍ ፈተና እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ረዲ፤ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ስለሆነ የሚዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተቋም ውስጥ ባሉ ባለሙያዎችም የእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ፈተና ይዘጋጃል።

ይሁን እንጂ ኤጀንሲው ፈተናውን የመረከብ፣ የማሰራጨት፣ የማረም እና ውጤት የመግለፅ በአጠቃላይ የማስተዳደር ኃላፊነት አለው። እርሳቸው እንደገለፁልን የ12ኛ ክፍል የፈተና የመልስ ቁልፍም የሚመጣው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው።

ለመሆኑ ከፈተና ዝግጅት እስከ ውጤት የሚከናወኑ ተግባራት ምንድን ናቸው?

1.ቅድመ ጥንቃቄ

የፈተና ዝግጅቱ ቅድመ ጥንቃቄና ሚስጢራዊነቱ የሚጀምረው እያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ማን እንደሚያዘጋጀው ባለማሳወቅና ሚስጢራዊነቱን በመጠበቅ ነው ይላሉ- አቶ ረዲ።

ፈተናው በሚዘጋጅባቸው ጊዜያትም አገልግሎት ላይ ከሚውሉት ኮምፒዩተሮች መረጃ አፈትልኮ እንዳይወጣ ታስቦ ኔትወርክ አልባ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው።

ፈተናው ከተዘጋጀ በኋላም የሚቀመጥባቸው የፈተና ካዝናዎች አሉ።

በሕትመት ወቅትም የሚታተምበት ተቋም በደህንነት ካሜራ 24 ሰዓት ጥበቃ ይደረግለታል።

በመማተሚያ ቤቱ ሥራውን የሚያከናውኑት ባለሙያዎች በሥነ ምግባራቸውና በሥራ ብቃታቸው ለፈተና ሥራ ብቻ የተመረጡ ናቸው። እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚደረገው ከኤጀንሲው የተመረጡ ባለሙያዎችና የፌደራል ፖሊሶች ባሉበት ነው።

''ውጤቱ ለእኔ ደመወዜ ነው" ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ብሩክ እናት

ፈተናው ወደ 'ሚታተምበት ክፍል ምንም ዓይነት ነገር ይዞ መግባት የማይፈቀድ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ፍተሻና ቁጥጥር ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር ፈተና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በሚጓጓዝበት ወቅት በምርጫ ቦርድ ቁልፍ ታሽገው ነው። ተረካቢው አካልም ቃለ ጉባኤ ተፈራርሞ፤ ወደ ክልል ሲሄድም በፌደራል ፖሊስ ጥበቃ ተደርጎ ነው።

ፈተናው በወጣው መረሃ ግብር መሰረት ለተማሪዎች እስከሚሰጥ ድረስም እንዲቆይ የሚደረገው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው።

2.ግንዛቤ ማስጨበጫ (Orientation)

ከፈተናው ቀደም ብሎና በፈተናው ወቅት ተማሪዎች አስፈላጊ መረጃዎችንና የመልስ ምርጫቸውን በጥንቃቄ እንዲሞሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማብራሪያ ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጂ በልጅነት ምክንያት ትኩረት ባለመስጠትም ሆነ በመደናገጥ ስህተት ሲሰሩ ግን ያጋጥማል። ፈተናው ሲሰጥም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል።

3.ከየፈተና ጣቢያው የመልስ ወረቀቶችን መሰብሰብ

በዚህ ሂደት የፈተና ወረቀቶቹ ተሰብስበው በየትምህርት ዓይነቱ፣ በየክልሉና ዞኑ ይደራጃሉ።

ከተደራጁ በኋላ ከእርማት በፊት በወረቀት (Hard copy) የተሰበሰቡት የመልስ ወረቀቶች ስካን ተደርገው ወደ ሶፍት ኮፒ (Soft copy) ይለወጣሉ። ከዚያም በተቋሙ ዳታ ቤዝ (የመረጃ ቋት) ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል።

4.ቁልፍ ማስተካከያ (Key correction)

ተፈታኞች ስም ሲፅፉ ወይም በራሳቸው በተማሪዎቹ መሞላት የሚገባቸው ኮዶችን ሲፅፉ የሚሳሳቱ ካሉ ቁልፍ ማስተካከያ ይደረጋል።

በዚህ ሂደት ነው የፈተና ወረቀቶቹ ከአራሚዎቹ እጅ ጋር የሚነካኩት። ይህ ስህተት ከየመፈተኛ ጣቢያዎቹ የሚመጣ የተፈታኞች ስም ዝርዝር (Master List) ጋር ተመሳክሮ ይስተካከላል።

"እንደዚህ ዓይነት ስህተት የሚፈጥሩ ተማሪዎች በርካታ ናቸው" የሚሉት ዳይሬክተሩ "የራሳቸው ጉዳይ ብለሽ ብትተያቸው ዜጎች ናቸው" ሲሉ በዚህ ምክንያት ማስተካከያ እንደሚደረግ ገልፀውልናል። ለተቋሙ ጊዜ የሚወስድበትም ይህን የማስተካከል ሥራ ነው።

መልሱን ለማስተካከል ግን የሶፍት ዌሩም ስሪት አይፈቅድም። ለማስተካከል ቢታሰብ እንኳን የሚቻል አይደለም።

5.የእያንዳንዱ ፈተና የመልስ ቁልፍ

የመልስ ቁልፉ ሶፍት ዌሩ ውስጥ ከገባ በኋላ እያንዳንዱን ፈተና የማረም ሥራ ይጀመራል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሆነ የፈተና ማረሚያ ማሽኑ ፈተናውን ለማረም የሚወስድበት ጊዜ ብዙ አይደለም። ሂደቱ በፍጥነት ነው የሚከናወነው።

ይህንን የፈተና ማረሚያ ማሽን ያቀረበው ድርጅት ማሽኑ ያለዕክል የሚጠበቅበትን ተግባር እንዲያከናውን በየጊዜው ፍተሻ ያደርግለታል። አገልግሎት የማይሰጡና ያረጁ ማሽኖች እየተወገዱ በአዳዲስ ይተካሉ። በየወቅቱም በባለሙያዎች ክትትል ይደረግለታል። ስለዚህ "የሚያሰጋ ነገር የለም" ብለዋል- ዳይሬክተሩ።

ቅሬታዎች ...

በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት የስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሳይቀሩ በርካታ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው ቅሬታዎች ቀርበዋል።

በዚህ የትምህርት ዓይነት ላይ ከዚህ ቀደም ቅሬታ ቀርቦ እንደማያውቅ የሚናገሩት ባለሙያው በ2007 ዓ.ም ግን [ጊዜውን እርግጠኛ አይደሉም] በአስረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በታሪክ ትምህርት ላይ ተመሳሳይ ቅሬታ ተነስቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በወቅቱም ቅሬታዎች ቀርበው በባለሙያዎች ሲፈተሽ የመልስ ቁልፉ ወደ ማረሚያ ማሽኑ ሲገባ ስህተት መፈጠሩ ታውቆ፤ ከዚያ በኋላ ትክክለኛው የመልስ ቁልፍ ገብቶ እንዲታረም መደረጉንና ውጤቱ በድጋሚ እንደተገለፀ ይናገራሉ።

28 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች በፈተና ወቅት ወለዱ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ሾልኮ መውጣት እንዲሁም ውጤት ላይ ቅሬታ መሰማታቸው የተለመደ ሆኗል። በዚህም ምክንያት በፈተና ወቅት በመላ ሃገሪቱ ኢንተርኔት እስከ ማዘጋትም ደርሷል። ፈተና በድጋሚ የተሰጠበት አጋጣሚም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ይህንኑ ያነሳንላቸው ዳይሬክተሩ "ያኔ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ነበር፤ ፈተናው እያንዳንዱ የአገሪቱ ጫፍ እስከሚደርስ ድረስ የተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ነበሩ" ይላሉ።

ነገር ግን በትክክል በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ጉዳይ በሕግ የተያዘ ስለሆነ እርሱ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ታዲያ አሁን ያለው ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዲፈጠር የሚያደርግ አይደለም ነው የሚሉን? ስንል ለዳይሬክተሩ ጥያቄያችንን አስከተልን።

"ከቀደመው ጋር ሲነፃፀር ሰላማዊ ነው ማለት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም" ሲሉ መልሰዋል።

በፈተና ውጤት ዙሪያ በክልሎች ደረጃ ቅሬታ ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን እንደ ግለሰብ ግን በየዓመቱ ቅሬታዎች እንደሚቀርቡና እንደሚታይላቸው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

ቢቢሲ ረቡዕ እለት ያነጋገራቸው የሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገ/እግዚአብሄር በበኩላቸው፤ በውጤቱ ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች በሙሉ አስፈላጊው ማጣራት ከተካሄደ በኋላ ምላሽ ይሰጠዋል ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ