ኤርትራ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ የጤና ተቋማትን ወሰደች

አሥመራ Image copyright Getty Images

ከኤርትራ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር የሚገኙ የህክምና መስጫ ማዕከላት ለመንግሥት ተላልፈው እንዲሰጡ ተወስኗል።

በያዝነው ሳምንት የህክምና ማዕከላቱ አስተዳዳሪዎች ለመንግሥት አሳልፈው መስጠታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዲፈርሙ መጠየቃቸውን የቢቢሲ ትግርኛ ክፍል ከኤርትራ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ንግድ ተጧጡፏል

ነገር ግን አብዛኛዎቹ የማዕከላቱ አስተዳዳሪዎች ሰነዱ ላይ ለመፈረም አለመስማማታቸውንና ከቤተክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች ጋር እንዲነጋገሩ መጠየቃቸው ታውቋል።

ይህን ተከትሎም ወታደሮች ሰራተኞቹን በማስወጣት ማዕከላቱን መዝጋታቸው ተገልጿል።

እስካሁን ድረስ የኤርትራ መንግሥት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ የኤርትራ ካቶሊክ የሃይማኖት አባቶች ለሁሉም ሰው ፍትህን ለማረጋገጥ በማለት ሃገራዊ የእርቅ ሂደት እንዲጀመር ጠይቀው ነበር።

መስመር ያልያዘው የኢትዮ-ኤርትራ የንግድ ግንኙነት ወዴት ያመራል?

ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሃይማኖት አባቶቹ በጻፉት ባለ 30 ገጽ ደብዳቤ ሃገሪቱ አንድ መሆን እንዳለባትና እርቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ነበር።

መንግሥት ማሻሻያዎችን እንዲያደርግና ህዝቡ ሃገሩን ለቅቆ የመሄድ ፍላጎት እንዳይኖረው እንዲሰራም ጠይቀው ነበር።