ጠብ አጫሪና ጥቃት አድራሽ የፌስቡክ ፖስቶችን እንዴት ሪፖርት ማድረግ ይቻላል?

Facebook logo Image copyright SOPA Images

የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሆነ ብለውም አልያም በስህተት የሚያሰሯጯቸው መረጃዎች በሌሎች ተጠቃሚዎች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በኢትዮጵያም ፌስቡክን በመጠቀም የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች በሌሎች ተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት ሲያስከትሉም ተስተውሏል።

የማህበራዊ ሚዲያ አውታሩ ፌስቡክም መሰል መረጃዎች በሌሎች ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመቅረፍ በማሰብ ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ በገፁ ላይ የሚመለከታቸው መልዕክቶች (Facebook posts) በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለው ከገመቱ ጉዳዩን ለፌስቡክ ሪፖርት የሚያደርጉበት ቀላል አማራጭ አቅርቧል።

ፌስቡክና ትዊተር ሐሰተኛ አካውንቶችን ሊያጋልጡ ነው

በሃሰተኛ ዜናዎች "የሞቱ" የኪነጥበብ ሰዎች

ለመሆኑ በሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የፌስቡክ መልዕክቶች የትኞቹ ናቸው?

የሚከተለው ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በተጠቃሚዎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ፌስቡክ ሪፖርት ሊደረጉልኝ ይገባል ይላል። መልዕክቶቹ በጽሁፍ፣ በፎቶ ወይም በቪዲዮ ሊቀርቡ ይችላሉ።

  • የጥላቻ ንግግሮች: ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርን ሰዎችን በብሄራቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በጾታቸው እና በአካል ጉዳተኝነታቸው በመለየት ከሰዋዊ ክብራቸው ዝቅ የሚያደርግ እና የሚያዋርድ ጥቃት ሲል ይገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችን ከገጹ ላይ ያስወግዳል።
  • ሐሰተኛ ዜናዎች፡ ሐሰተኛ ዜና ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ወይም የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት የሚሰራጭ የውሸት መረጃ ማለት ነው። በርካቶች የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ሐሰተኛ መረጃዎችን እውነት በማስመሰል ያሰራጫሉ። በሃገራችን ፌስቡክን በመጠቀም የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለበርካታ ጥፋቶች መንስዔ መሆናቸው ይታወሳል። ፌስቡክም ከተጠቃሚዎቹ በሚደርሰው ሪፖርቶች መሠረት አስፈላጊውን ማጣራት ካካሄደ በኋላ ሐሰተኛ መረጃዎቹን ከገጹ ያጠፋል።

'ሃሰተኛ ዜና '፡ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ስጋት?

አይሸወዱ፡ እውነቱን ከሐሰት ይለዩ

  • ልቅ የሆኑ ምስሎች እና ቪዲዮዎች፡ ፌስቡክ ልቅ የሆኑ የግብረ-ስጋ ግነኙነትን እና እርቃንን የሚያሳዩ ቪዲዮችን እና ምስሎችን ያግዳል። ለዚህም እንደምክንያት የሚቀርበው እንደዚህ አይነት የአደባባይ መልዕክቶች ከማህበረሰቡ እሴት ጋር አብሮ አይሄድም የሚል ነው። በተጨማሪም ቪዲዮዎቹ እና ምስሎቹ የተገኙት በፍቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ግነኙነት ስለመሆኑ ማረጋገጫ አይገኝላቸውም።
  • ሽብር የሚነዙ መልዕክቶች፡ የሸብር ጥቃትን ወይም ሽብርተኛን የሚያወድሱ፣ የሽብር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ወይም የሽብር ቡድን አባልነት ጥሪ የሚያደርጉ፣ በሽብር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ላይ የሚያፌዝ የፌስቡክ መልዕክቶች በፍጥነት እንዲጠፉ ይደረጋሉ። ተጠቃሚዎች ይህን አይነት ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ሪፖርት እንዲያደርጉ ፌስቡክ ይጠይቃል።
  • ኃይል የተሞላበት ጥቃትን የሚያሳዩ መልዕክቶች፡ ፌስቡክ ኃይል የተሞላበት ጥቃትን የሚያገኑ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያዋርዱ መልዕክቶችን ያስወግዳል።
  • ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በፌስቡክ ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም።

ከላይ የተጠቀሱትን አይነት ይዘት ያላቸውን የፌስቡክ መልዕክቶች እንዴት ሪፖርት ማድረግ ይቻላል?

ቀላል ነው።

Image copyright Facebook

ለምሳሌ በምስሉ ላይ የሚታየው መልዕክት ይዘት በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል ብለን እናስብ።

ይህን መልዕክት ለፌስቡክ ሪፖርት ለማድረግ ከመልዕክቱ በስተቀኝ አናት ጋር የሚገኙ ••• (ሶስት ነጥቦች) መጫን። ሶስቱን ነጥቦች ስንጫን አራት አማራጮችን ይሰጠናል። ከዚያም የመጨረሻውን አማራጭ ማለትም ''በመልዕክቱ ላይ አስተያየት ይስጡ'' (Give feedback on this post) የሚለውን ይጫኑ።

Image copyright Facebook

''Give feedback on this post'' የሚለውን ሲጫኑ ከላይ የሚታየውን አይነት ሌላ አማራጭ ይሰጥዎታል።

ለምሳሌ የተመለከቱት የፌስቡክ ፖስት ወይም መልዕክት ሐሰተኛ ዜና ከሆነ፤ False news የሚለውን ይጫኑ። ከዚያም ጉዳዩን ፊፖርት በማድረግዎ ከፌስቡክ የምስጋና ምላሽ ያገኛሉ።

ይህን የፌስቡክን ስርዓት በመጠቀም በሰዎቸ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተጽእኖዎችን መቀነስ ይቻላል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ